Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል መሰብሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የምርት ዘመን እየለማ ከሚገኘው ሰብል ውስጥ እስከ አሁን 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል መሰብሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ አጀበ ስንሻው÷በምርት ዘመኑ ከ5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 160 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሩብ አመቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰቡን ጠቅሰው÷ ሰብልን በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በ2016 ሩብ አመት 102 ሺህ ኪዩቢክ ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ 25 ሺህ ኩንታል ሜትሪክ ቶን ማምረት ተችሏል ብለዋል።

በዚህ አመት ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት 40 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ የተገለጸ ሲሆን÷ከዚህ ውስጥ 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታሉ የበጋ ስንዴ ነው ተብሏል፡፡

ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር ለመፍታትም በፌደራል መንግስት ለክልሉ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ እንደቀረበም ተገልጿል፡፡

በምርጥ ዘር አቅርቦት 186 ሺህ 898 ኩንታል ቀርቦ 178 ሺህ 58 ኩንታሉን ማሰራጨት ተችሏልም ነው የተባለው።

የእርሻ ሜካናይዜሽንን ለማስፋት በተደረጉ ጥረቶች ካለፈው አመት ጀምሮ 303 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደተቻለም ቢሮው ገልጿል፡፡

ቢሮው የሩብ አመት አፈፃፀም ግምገማ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ሲሆን÷የክልልና የዞን የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎችም ተገኝተዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

Exit mobile version