Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ በሆርቲካልቸርና በእንስሳት ልማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የተፈረመው ስምምነት 3ኛው ምዕራፍ “ሆርቲ- ላይፍ” ፕሮጀክት ሆርቲካልቸር ልማት ላይ እንዲሁም 2ኛው ምዕራፍ “ብሪጅ ፕላስ” ፕሮጀክት ደግሞ የወተት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ÷የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ስራን ባለፉት የፕሮጀክቶቹ ምዕራፎች በገንዘብ በመደገፍ ውጤታማ አፈፃፀም መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ለኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግስት የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

“ብሪጅ ፕላስ” ፕሮጀክትም የመንግስትን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Exit mobile version