Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም በጤናው ዘርፍ የጤና ተቋማት መልሶ በመገንባትና በጥገና ከ95 በመቶ በላይ መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ተገለጸ፡፡

የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

በመድረኩ የጤና እና ማህበራዊ ዘርፍ አፈፃፀምን በሚመለከት በስፋት የተገመገመ ሲሆን፥ የየተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና የህፃናትን ጤና በመጠበቅና በቤተሰብ ዕቅድ አፈጻጸም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ክትባት አምልጧቸው የነበሩ 243 ሺህ ህፃናት መከተባቸውን ጠቅሰው፥ የእናቶችን ጤና በመጠበቅም ብዙ መሰራቱን አብራርተዋል።

ከወሊድ አገልግሎት ጋር በተገናኘ በ106 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በሩብ ዓመቱ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ቲቢንና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም የወባ ስርጭትን ለመግታት የተቀናጀ ምላሽ መስጠት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም፥ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ በመገንባትና በጥገና ከ95 በመቶ በላይ መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ17 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በበጎ ተግባራት 117 ሺህ ህፃናት ጎዳና ሳይወጡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው እንዲደገፉ መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡

አካል ጉዳተኞችኝ፣ አረጋውያንና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ በኩልም ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ የሴፍቲኔት ፕሮግራምም 1 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version