Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዳያስፖራ ፖሊሲን ለማሻሻል ጥናት ሊካሄድ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ላለፉት አስር ዓመታት ሥራ ላይ የዋለውን የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ፖሊሲ ለማሻሻል ተጨማሪ ጥናት ሊያካሂድ መሆኑን ገልጿል፡፡

የዳያስፖራ ፖሊሲን ለማሻሻል እየተከናወኑ ባሉ የጥናት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

የዳያስፖራ አገልግሎት ከጅማ፣ ከወሎ፣ ከሐዋሳና ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥናት ለማካሄድና የጥናቱን ውጤት ተከትሎ ፖሊሲውን ለማሻሻል በ2013 ዓ.ም የመግባቢያ ሥምምነት ፈጽሟል።

በዚህም በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ ከቆየው ጥናት በተጨማሪ በወሎ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ተጨማሪ ጥናት ለማካሄድ ዛሬ ከሥምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡

ጥናቱ ለቀጣይ 8 ወራት የሚካሄድ ሲሆን÷ የሁለቱን ጥናት ውጤቶች ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲ ማሻሻያ ሥራ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር)÷ ፖሊሲውን በመረጃና ጥናቶች ላይ ተመስርቶ ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያው ዳያስፖራው በሀገር ቤት የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲያስችለው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሚካሄድ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ዳያስፖራው ያለውን የሙያ አቅምን ከግምት ባስገባ መልኩ ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት በማለም ማሻሻያው እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡

Exit mobile version