Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጭንቅላት እጢ ወይም እብጠት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አብዛኛዎቹ የጭንቅላት (አንጎል) እጢ ወይም ተመሳሳይነት ያለው የአንጎል እብጠት ያላቸው ሰዎች የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡

ከእነዚህ ምልክቶች ውስጥም፡-

1. ራስ ምታት:- በአብዛኛው እጢ ያላቸው ሰዎች ላይ የሚኖር ምልክት ሲሆን÷ ረጅም ወይም አጭር ጊዜ የቆየ በቀላል ማስታገሻ በደንብ የማይቀንስ፣ ጠዋት ከእንቅልፍ ሲነሱ፣ ሲያጎነብሱ፣ ሲያስሉ የሚጨምር ራስ ምታት ይኖራቸዋል፣

2. የእይታ ችግር:- የዓይን የእይታ መቀነስ (እየባሰ የሚሄድ)፣ ከፍሎ መጨለም፣ ብዥታ፣ አንድ ነገር ሁለት ሁኖ መታየት፣ የዓይን መርገብገብ፣ የዓይን መንሸዋረር ቀላል በማይባሉ ሰዎች ላይ የሚያጋጥም ምልክት ነው፣

3. የሚጥል በሽታ:- ሁሉም የሚጥል በሽታ ያላቸው ሰዎች በእጢ ወይም በተመሳሳይ እብጠት ምክንያት ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ግን የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው እጢና ከእጢ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የአንጎል እብጠት አለመኖሩን በምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣

4. የሰውነት መስነፍ:- ይህ ምልክት አንድ እጅ ወይም አንድ እግር ወይም በአንድ በኩል እጅና እግር (ግማሽ ሰውነትን ከፍሎ) ወይም ሁለቱም እግር መስነፍ ወይም ሙሉ በሙሉ አልታዘዝ የማለት ችግር መኖር ማለት ነው፣

5. መንገዳገድ፡- መንገድ ሲራመድ (ስትራመድ) መስመር አለመጠበቅና ይህ ለማካካስ እግር ሰፋ አድርጎ መርገጥና መራመድ፣ ወደ አንዱ አቅጣጫ (ወደ ፊት) ወደ ኋላ የመውደቅ አዝማሚያ ይኖራቸዋል፣

6. መስማት መቀነስ:- አዲስ ወይም ቀስ በቀስ እየባሰ የሚሄድ የመስማት ችግር፣ ጆሮ ውስጥ የጩኸት ስሜት መኖር ሊኖራቸው ይችላል፣

7. ሽንት ወይም ሰገራ አለመቆጣጠር፡- ሽንት ብቻ ማምለጥ፣ ሰገራ ብቻ አለመቆጣጠር ወይም ሁለቱንም ያለመቆጣጠር ችግር ሊኖር ይችላል፣

8. ትንታ:- ውሃ ወይም ሌላ ፈሳሽ ነገር ሲወሰድ ተደጋጋሚ የሆነ ትንታ መኖር እና ከዚህ ጋር በተያያዘም የሳንባ ኢንፌክሽን መፈጠር፣ በተደጋጋሚ ሳል ማሳል ሊኖር ይችላል፣

9. ማስመለስ:- ከአንጎል እጢ ወይም ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ችግሮች የሚኖረው ማስመለስ ከማቅለሽለሽ ጋር ያልተያያዘ (ያለማቅለሽለሽ)፣ ድንገት የሚመጣ ሲሆን÷ ብዙ ጊዜ አብሮ ራስ ምታት ይኖራቸዋል፣

10. የመናገር ችግር:- እንደ እጢው ወይም እብጠቱ ያለበት የአንጎል ክፍል፣ ምንም መናገር አለመቻል፣ ሰው የሚናገረውን ሐሳብ አለመረዳት፣ ሲናገሩ መኮላተፍ፣ የተናገሩትን ነገር ደግሞ አለመናገር ሊኖራቸው ይችላል፣

11. የማስታወስ ችግር (መርሳት)፡- የቅርብ ወይም የረዥም ጊዜ ኩነት የማስታወስ ሁኔታ መቀነስ፣ ሰው፣ ቦታ፣ ጊዜ ያለማስታወስ ሁኔታም ሊኖራቸው ይችላል፣

12. የፊት እና አገጭ ላይ ከባድ ህመም ወይም የመደንዘዝ ስሜት፡- እንደ እጢው ባህሪ አብዛኛው ጊዜ የተወሰነ የፊት ክፍል ወይም አገጭ ላይ ወይም ሙሉ ግማሽ ፊት ላይ ቶሎ ቶሎ የሚመላለስ ከባድ የሆነ ህመም ወይም የመደንዘዝ ስሜት ሊኖር ይችላል፣

13. የንቃት መቀነስ:- የአንጎል እጢ ያለበት ሰው የንቃት ደረጃው መቀነስ በደንብ ካለማውራት እስከ ምንም አለመናገር ሊደርስ ይችላል፣

14. የጭንቅላት መጠን መጨመር:- እጢ ወይም ተመሳሳይ እብጠት እና ከነዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር ያላቸው ልጆች ላይ ከልክ ያለፈ የጭንቅላት እድገት ሊኖር ይችላል፣

15. ከልክ ያለፈ የሰውነት መጠን መጨመር:- አዲስ የሆነ ከልክ ያለፈ ክብደት መጨመር፣ ከልክ ያለፈ ቁመት፣ ከልክ ያለፈ የእጅ እና የእግር፣ የአገጭ መግዘፍ ሊያጋጥም ይችላል፣

16. የማሽተት አቅም መቀነስ:- ይህ በአብዛኛው ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዙ ኢንፌክሽን ወይም ሌላ ኩነት የሚከሰት ነው። እጢ ከሆነ ከዚህ ችግር ጋር ተያይዞ ራስ ምታት፣ የፀባይ ለውጥ፣ የእይታ ችግር ወይም ሌላ ምልክት ይኖራቸዋል፣

17. ምንም ምልክት አለመኖር፡- ለሌላ ተብሎ በተሰራ ምርመራ አጋጣሚ የአንጎል እጢ ሊገኝ ይችላል።

የእጢው እድገት እና ባህሪ ታይቶ ኦፕራስዮን ወይም ሌላ የሕክምና አማራጭ ሊያስፈልገው ስለሚችል ክትትል ማድረግ ይገባል።

Exit mobile version