Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱና ሰላም እንዲመጣ ሁሉም መሥራት ይገባዋል – ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱና ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት ይገባዋል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ እዝ አዛዥ ሌtናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ጄኔራል መኮንኖች በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝበ ሰላም ነው፤ የቆምነው ለሠንደቅ ዓላማ እና ለኢትዮጵያ ነው ብለዋል፡፡

እኛ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነን፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ደግሞ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለሕዝብ ሰላም ይሠራል ያሉ ሲሆን÷ ሕዝቡ ለሰላም እንዲሠራም አሳስበዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባውም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የራስ ሃሳብን ብቻ የሚያራምድ እና ሌሎችን የማይቀበል አካሄድ ሀገር የሚያፈርስ መኾኑን ገልጸው፤ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ሰከን ብሎ በማሰብ ክልሉን ወደ ሰላም መመለስ ይገባል ያሉት ደግሞ የሰሜን ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ናቸው፡፡

ሰራዊቱ ለአማራ ሕዝብ ታላቅ ክብር አለው ያሉ ሲሆን÷ ባልተገባ መንገድ ሕዝብ ማወናበድ ሕዝብን ለመከራ ይዳርጋል፤ የሕዝብን መከራ ለማቃለል እውነትን መሠረት በማድረግ መነጋገር ይገባል ነው ያሉት።

Exit mobile version