አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 125ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሩሲያ የባህል ማዕከል ተከብሯል፡፡
‘ፋውንዴሽን ፎር ክርኤቲቭ ኢኒሺዬቲቭ’ ከሩሲያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል ሳይንሳዊና ትምህርታዊ ዝግጅቶችን አካሂዷል።
የሩሲያ-ኢትዮጵያ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን መሠረት ያደረገ ከሥልጣኔ ጋር የተያያዘ ውይይትም ተካሂዷል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የሁለቱ ሀገራት የህዝብ፣ የዲፕሎማሲ እና የትምህርት ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል የባህል፣ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር ተደርጓል።
በሁለቱ ሀገራት የትምህርት እና የምርምር ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ማጠናከር በሚቻልበት፣ የህዝብና የግል አጋርነት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ በአፍሪካ ማጎልበት በሚቻልባቸው ዘዴዎች ዙሪያም በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
የሩሲያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችም ከኢትዮጵያ ጋር ልምድ ለመካፈል በማሰብ በሩሲያ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ሩሲያ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ላይ ያተኮሩ ገለጻዎች አቅርበዋል።
የንግድ ሥራን ማስተዋወቅ እና በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች መካከል የረጅም ጊዜ ትብብር መፍጠርም በመድረኩ ዋና አጀንዳ ነበር።
በዝግጅቱ ላይ ሩሲያ እና ታዋቂ ሰዎቿ በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ኢኮኖሚ እና ጤና አጠባበቅ ላይ ያበረከቱትን አስተዋፅዖም አስመልክቶ ገለጻ ቀርቧል።
“ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ከቅኝ አገዛዝ እና ከኒዮ-ቅኝ አገዛዝ ጋር የተደረገው ትግል፣ የታሪክ ልምድ እና የወደፊት አጀንዳ” እንዲሁም “የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዘመናዊው ዓለም፣ የብዝሃ-ዋልታ ጽንሰ-ሀሳብ” በሚል ርዕስ የተደረጉ ገለፃዎችም ነበሩ።
ኢትዮጵያ ወደ (ብሪክስ) የኢኮኖሚ ህብረት የመቀላቀል ፋይዳና በሩሲያ እና በኢትዮጵያ መካከል እያደገ ያለው የንግድ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ኢንቨስትመንት ትስስር ተስፋም በዝግጅቱ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
በአዲስ አበባ የሩስያ ፌደሬሽን ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሚካሂል ኮርኔቭ በባህል፣ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ሀገራቱ የተፈራረሟቸው ስምምነቶችና የትብብር ዘርፎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ