Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዩኒቨርሲቲዎች የተጠናከረ የአካዳሚ ነጻነት እንዲኖር እየተሰራ ነው – ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት እና የተጠናከረ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲኖር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ነጻነት” በሚል ሀሳብ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንደገለጹት÷ የዩኒቨርሲቲዎችን አካዳሚክ ነጻነት ማረጋገጥ በትምህርት ሴክተሩ እየተከናወኑ ካሉ የሪፎርም ስራዎች መካከል አንዱ ነው።

የዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝነት ዓላማ አካዳሚያዊ ነጻነትን ማረጋገጥ ሲሆን÷ በዚህም ረገድ አካዳሚክ ፕሮግራሞችን በነጻነት የመቅረጽና የመተግበር፣ የተማሪዎችን የመመልመያ ስርዓቶችን መደንገግና ሌሎች የአሰራር ነጻነቶች እንዲኖሩ ማድረግ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ሆነው የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳት ተነጋግረው የሚወጡበት መድረክ መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት እውነተኛ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲኖር መንግስት በቁርጠኝነት የያዘው አቋም ነው ብለዋል።

የራስ ገዝነት ሂደቱ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንደሚሆኑ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)÷ የዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑ ልዩ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።

ራስ ገዝ መሆኑ ለአካዳሚው ነጻነት መሠረት የሚጥልና የትምህርት ጥራትን እንዲሁም የምርምር ውጤታማነትን ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።

Exit mobile version