አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራር ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ ሊሰራበት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡
የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራት ሽግግር የመጀመሪያው ጉባዔ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ “በክልሉ የታየው የትምህርት ጥራት ጉድለት የአመራር ሰጪነት ሚናችንን በአግባቡ ያለመወጣችን ውጤት ነው”።
በመሆኑም ከክልል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያለው አመራር ትኩረት አድርጎ ከሚያስፈፅማቸው አጀንዳዎች መካከል የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው ይሆናልም ነው ያሉት።
ይህን ለመከታተልም የትምህርት ጥራት ጉባዔ ከክልል ጀምሮ በዞኖች፣ በከተማዎች፣ በወረዳዎች፣ በቀበሌዎችና ትምህርት ቤቶች ድረስ እንደሚቋቋምም ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ስምንት አጀንዳዎች ተለይተው በትኩረት ይሰራባቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ በተለይም የፖለቲካ አመራሮች በእያንዳንዱ ት/ቤት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ዋነኛው ስራ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
አክለውም፥ መምህራን የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለመደገፍና ለመከታተል እንዲሁም በተማሪ ስነ- ምግባርና የትምህርት ቤቶች ጥራት የሚከታተል ቦርድ ማደራጀት ላይ ይሰራል ሲሉም ነው የተናገሩት።
በተመሳሳይ በክልል ደረጃ አዲስ የመምህራን ሙያ ምዘናና ብቃት ማረጋገጫ አሰራር፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የመምህራንና ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በሙሉ አቅም ተግባራዊ ከሚደረጉት ጉዳዮች ዋነኞቹ መሆናቸውን አክለዋል።