አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ 170 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ማዕድን በማውጣትና ፍለጋ ሥራ ላይ እንደሚገኙ ማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዮስ እንደገለጹት ፥ ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ኃብት ያላት ሀገር ብትሆንም አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል በቂ ተግባራት ባለመከናወናቸው ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን ያህል ድጋፍ ሳያደረግ ቆይቷል።
መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸውና የሀገሪቱን እድገት ያፋጥናሉ ተብለው ከተለዩ አምስት ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በዋናነት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለመሳብ መንግሥት የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም 70 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የማዕድን አውጪ ኩባንያዎች፣ በኢትዮጵያ ማዕድን እንዳላቸው በተረጋገጡ አካባቢዎች ላይ የማልማት ሥራ እያከናወኑ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም 100 ኩባንያዎች ጥናትን መሠረት በማድረግ የማዕድን ፍለጋ ሥራ ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በማዕድን ልማት ላይ ያሉ ኩባንያዎች ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ማዕድን ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

