Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ቅጥር ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ በመጠቀም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ዲስትሪክት የሥራ ቅጥር ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ።

ተከሳሾቹ የዋስትና መብታቸው ታግዶ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተከሳሾቹን የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ድንጋጌን ተላልፈዋል በማለት ሀሰተኛ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሰነዶችን አዘጋጅቶ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር፡፡

ክሱ የቀረበባቸው ተከሳሾች አጠቃላይ 12 ሲሆኑ፥ ከተከሳሾች መካከል ባጂጌ ከበደ፣ ግርማዬ ደገፉና በሬዳ ነበራ ይገኙበታል።

በቀረበው ክስ ላይ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ዲስትሪክት በወጣ የሥራ ማስታወቂያ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ የሥራ ቅጥር ውል ስምምነት መፈጸማቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ከተከሳሾቹ መካከል አሥሩ የቅጥር ውል ከፈጸሙ በኋላ ለ10 ወራት በየደረጃው በተለያዩ መጠን ወርኃዊ ደመወዝ መውሰዳቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።

ቀሪዎቹ ማለትም ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የሥራ ቅጥር ውል ስምምነት ከፈጸሙ በኋላ የማስረጃ ማጣራት ሥራ ሲጀመር መሰወራቸው ነው ዐቃቤ ሕግ በክሱ የጠቆመው።

በዚህም ዐቃቤ ሕግ ሀሰተኛ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሰነዶችን አዘጋጅቶ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ክስ ዝርዝር ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን፥ በችሎቱም የክስ ዝርዝሩን በንባብ አሰምቶ ነበር።

በዚህ ክስ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብት ጥያቄ ሲያነሱ፥ ዐቃቤ ሕግ ዋስትና መብታቸው ሊገደብ ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ ክርክርን መርምሮ የተከሳሾቹን ዋስትና በመገደብ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ አዟል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር እንዲሻሻልላቸው ጠቅሰው፤ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግም ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ክሱ ግልጽ መሆኑን ጠቅሶ፤ ሊሻሻል አይገባም የሚል መልስ በጽሁፍ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግ መልስን መርምሮ ዛሬ ከሰዓት በዋለው ችሎት ቀጠሮ ተከሳሾቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ክሱ እንዲሻሻል የሚያስችል የህግ መሰረት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

የተከሳሾቹን የዕምነት ክህደት ለመቀበልም ለሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version