Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያን ከሕክምና ግብዓቶች ጥገኝነት ለማላቀቅ የሀገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመድሐኒትና የሕክምና ግብዓቶች ፍላጎትን ለሟሟላትና የውጪ ጫናን ለመቀነስ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚው ከዘርፉ አጋር አካላት ጋር በመሆን በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፖርክ በሚገኙ የመድሐኒትና የሕክምና ግብዓት አምራቾች የሥራ ሁኔታ ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

በመስክ ምልከታው ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በምልከታው በኢንዱስትሪ ፖርኩ የሚገኙ ሶስት የመድሐኒትና የህክምና ግብዓት አምራቾች የተጎበኙ ሲሆን፥ በዚህ ወቅትም አምራቾቹ የሚገኙበትን ደረጃና በዘርፍ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና ግብዓት አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶላ፥ አምራቾች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከሟሟላት ባሻገር ኢትዮጵያን በዘርፉ ቀዳሚ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

በፖርኮች የመሠረተ-ልማት አለመሟላት፣ ለመድኃኒት ማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶች የታክስ ጫናና የመንግሥት የግዢ ሥርዓት የሀገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ አለመሆኑ በሚፈለገው ልክ እንዳንሰራ አድርጎናል ብለዋል።

ጠንካራ የውጭ ጫናዎችን የሚቋቋም የጤና ሥርዓት ለመገንባት መንግሥት የገበያ ዕድሎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፖርክ 187 አልሚዎች ለመቀበል የሚያስችል አቅም እንዳለው የተገለፀ ሲሆን፥ ከ200 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማቅረብ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው፥ አምራቾች እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

Exit mobile version