Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሁኔታ ላይ እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ÷ የተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በክልሉ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመከላከያ ሠራዊትና በክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ አጠቃላይ አመራሩና ሰላም ወዳዱ ሕዝብ በቅንጅት የሰሩት ስራ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም እንዲገኝ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በተከታታይ የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች መከናወናቸው አሁን ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስተዋል ።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት ይቻል ዘንድ ወቅቱን እና ሁኔታዎችን ያገናዘበ የጋራ አመራር የመስጠትና የማረጋገጥ ተግባር ከመላው አመራር እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡

“ሕዝባችንን ካለበት ችግር ውስጥ በፍጥነት ለማውጣት ከወትሮው የተለየ ስራ ይጠይቃል” ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሰሞኑ በተደረጉ የውይይት መድረኮች ያገኘናቸውን ገንቢ እና ተራማጅ ሀሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር የክልሉን የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይኖርብናልም ብለዋል።

Exit mobile version