Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮምቦልቻ ለተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮምቦልቻ ከተማ የአዲስ አበባ ባለሃብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር ለሚገነባው የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷በወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ከሁሉም የሀገራችን ክልሎች የመጡ የመንግስት አመራሮችን የማስፈፀም አቅም ለመገንባት በሚሰጠው ስልጠና ላይ ተገኝቼያለሁ ብለዋል።

ስልጠናው የአመራርን አቅም ከመገንባት ባሻገር ሰልጣኞቹ ይበልጥ እንዲቀራረቡና እንዲተዋወቁ ዕድል እንደሚያመቻችላቸው እንዲሁም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን እንደሚያጠናክርላቸውም ገልጸዋል፡፡

ከስልጠናው በኋላ የለውጡ ትሩፋት የሆነውን የሰው ተኮር ስራ ልምዳችንን ለማካፈል እንዲሁም ወንድማማችና እህትማማችነትን ለማጠናከር በኮምቦልቻ ከተማ የአዲስ አበባ ባለሃብቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር ለሚገነባው የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ አስቀመጥናልም ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እንደጎበኙ ጠቅሰዋል፡፡

የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን የሚቆጥቡ ተኪና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን በጥራት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እየተበራከቱ እና አቅማቸውን እያሳደጉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል፡፡

የጀመርነው የብልፅግና ጉዞ በሁላችንም ትጋት እንዲሳካ በትብብርና በጋራ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

 

 

Exit mobile version