Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

155 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ከኢቱ ጎሳ ማኅበረሰብ ጋር በፀጥታ ጉዳይ ላይ ባደረገው ውይይት 155 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸው ተገልጿል፡፡

በኅብረተሰቡ ውስጥ መሽገው በህቡዕ በመንቀሳቀስ ራሳቸውን የገንዘብና ሃብት አሰባሳቢ ቡድን፣ የሰብዓዊ መረጃ ቡድን፣ የቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ክንፍ፣ የአፈናና ስወራ ቡድን አባላት ብለው በማደራጀት በተለያየ ወቅት የተለያየ የሽብር ተግባራትን በመፈፀም የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ መቆየታቸው ተጠቅሷል፡፡

በሐይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በአካባቢው ማኅበረሰብ በጎ ተፅዕኖ ምክንያት ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው የተመለሱት የሽብር ቡድኑ አባላት ለሽብር ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን የተለያዩ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችና ሞተር ሳይክሎች ለሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ማሥረከባቸውን የክፍለ ጦሩ አዛዥ ገልፀዋል፡፡

የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮሎኔል አሕመድ ኢሚ ኅብረተሰቡ የራሱ የሰላም ዘብ መሆን በመጀመሩና ከሰራዊታችን ጋር በትብብር በመስራቱ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መረጋጋት እየታየበት ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኅብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቅንጅት የፀጥታ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version