አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የመረጃ ክትትል እና ትንተና ቡድን መሪ አቤል ጌታቸው እና ነጋዴ በሆኑት አቶ ፉፋ ዳባ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላለፈባቸው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አጠቃላይ ሁለት ክሶችን አቅርቦ ነበር።
አቤል ጌታቸው በተባለው ግለሰብ ላይ የቀረበው ክስ ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ክስ ነበር።
በዚህም ክስ ላይ የተመለከተውን አቶ አቤል ጌታቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ውስጥ የመረጃ ክትትልና ትንተና ቡድን መሪ ሆኖ ሲሰራ የተቋሙን አሰራር ባልተከተለ መልኩ የባለሀብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት ለባለሀብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ክስ እንደሚመሰረትባቸው በመግለጽ ያስፈራራቸው ነበር በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
አጠቃላይ ተከሳሹ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶችን አስቀድሞ በማጥናትና በመምረጥ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት ባለሀብቶችን በማስፈራራት ከ3 ግለሰቦች በአጠቃላይ 3 ሚሊየን 70 ሺህ ብር ገንዘብ ፉፋ ዳባ በተባለው 2ኛ ተከሳሽ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሷል።
ሁለተኛ ተከሳሽን ፋፋ ዳባ በሚመለከትም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ፣ለ ፣ሐ ስር ያለውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በወንጀል የተገኘ 3 ሚሊየን 70 ሺህ ብር የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ በስሙ በባንክ የገባውን ገንዘብ በተለያዩ መጠን በመጠቀም ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
በዚህ መልኩ ክሱ ለተከሳሾች ከደረሰና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ተከሳሽ ፉፋ ዳባ ላይ የቀረበው የክስ ድንጋጌ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ በዋስ በውጭ ሆኖ እዲከታተል ብይን ሰጥቶ ነበር።
አንደኛ ተከሳሽ አቤል ጌታቸውን በሚመለከት ግን የዋስትና መብቱ ተገድቦ ማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል ብይን በመሰጠቱ ከማረሚያ ቤት እየቀረበ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ አምስት ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ይሁንና ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ በዋስ ከእስር ተፈቶ በውጭ ሆኖ ጉዳዩን የሚከታተለውን ሁለተኛ ተከሳሽን በሚመለከት የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በልደታ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በሌላ ችሎት በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተከሰሱት የፋይናንስ ደህንነት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ቴድሮስ በቀለ በተከሰሱበት አንደኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል።
በታሪክ አዱኛ