Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው ውይይት አራተኛው ዙር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አራተኛው ዙር ውይይት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና በልማት አጋሮች መካከል ከገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር ተካሂዷል።
 
በፈረንጆቹ ሕዳር 29 ቀን 2023 በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የተካሄደው ውይይት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰመሪታ ሰውሰው፣ የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) እንዲሁም አምባሳደሮችና የኤምባሲ ተወካዮች ተገኝተዋል።
 
ውይይቱም ኮሚሽኑ የደረሰበትን ደረጃ ለአጋር አካላት ለማስገንዘብ ያለመ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
 
ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለሚያደርገው ጥረት በበተመድ የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በኩል ከተለያዩ የልማት አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኝ መቆየቱም ተገልጿል።
 
በአሁኑ ወቅት ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎችን በማዘጋጀት፣ ተሳታፊዎችን በመለየት እና የውይይት አመቻቾችን አቅም ለማጎልበት ኮሚሽኑ በመሠረታዊ ደረጃ በመመካከር ላይ እንደሚገኝ በውይይት መድረኩ ተገልጿል።
 
በውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችም ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እና ሌሎች ኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ለዚህ ስራ መንግስት ከያዘው በጀት በተጨማሪ ከአጋር አካላት 35 ሚሊየን ዶላር ገቢ ሊደረግለት ታስቦ 13 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱም ተጠቁሟል።
 
ውይይቱ ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ጠቃሚ መድረክ እንደሆነ ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ለሀገራዊ የምክክር ሂደት እውን መሆን የአጋር አካላት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ጠቃሚ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version