Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሕገ-ወጥ መንገድ ፓስፖርት ከመስጠት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 13 ግለቦች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለውጭ ሀገር ዜጎች ተሰጥቷል በተባለ ሕገ-ወጥ ፓስፖርት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ደላሎች ናቸው የተባሉ 13 ግለቦች ላይ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቀደ።

ከፓስፖርት እና ቪዛ ድለላ ተግባር ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ጳውሎስ ጌታሁን እና ዳንኤል ጥላሁንን ጨምሮ አጠቃላይ 13 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

ፖሊስ በነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን ተከትሎ የምርመራ መዝገቡን ሕዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ገልጿል።

ተነጥሎ መዝገባቸው ሲታዩ የነበሩትን ጨምሮ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ የሰጠ ሲሆን፤ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግም መዝገቡን መረከቡን አረጋግጧል።

ከምርመራ መዝገቡ ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን ተመልክቶ በክስ አመሰራረት ላይ ለመወሰን እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን የሚከታተሉት ዳኛም ተጠርጣሪዎቹ ክሱ እስከሚመሰረትባቸው ድረስ በእስር የሚቆዩበት ምክንያት አልቀረበም የሚል ጥያቄ ለዐቃቤ ሕግ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በእስር የሚቆዩበት ምክንያት በጽሑፍ ከቀረበው አቤቱታ ላይ አያይዞ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በከባድ የሙስና ወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚያስችሉ ማስረጃዎች አሉ ያለው ዐቃቤ ሕግ÷ እስከ 10 ዓመትና በላይ በሚያስቀጣ ዋስትና በሚያስከለክል ከባድ ሙስና አዋጅ ድንጋጌ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከመንግስት ሰራተኞችና አመራሮች ጋር በመመሳጠር የተሰራውን የወንጀል ድርጊትን በሚመለከት የሰነድ ማስረጃዎች እንዳሉትም ነው ዐቃቤ ሕግ ያስረዳው፡፡

በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት የልደት ካርዶች፣ ሕገ-ወጥ ፓስፖርቶች እና የተለያዩ ሰነዶች መገኘታቸውንም ገልጿል።

የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች በአንድ ፓስፖርት ከ12 ሺህ እስከ 15 ሺህ ዶላር እየተቀበሉ በሕገ-ወጥ መንገድ ቪዛ እና ፓስፖርት በማዘጋጀትና በመስጠት ደረጃ ከመንግስት ሰራተኞችና አመራሮች ጋር እንዲሁም ከደህንነትና ከኤምባሲ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በድለላ ተግባር ተሳትፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎችን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መኖራቸውን ዐቃቤ ሕግ አብራርቷል።

በዚህ መልኩ ሌሎች በተመሳሳይ ወንጀል ምርመራ ሲደረጉባቸው የነበሩ መዝገቦች እንዳሉ ጠቅሶ፤ መዝገቡን ተመልክቶ ለመወሰን የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በየደንበኞቻቸው የተወከሉ አራት ጠበቆች ደግሞ የዐቃቤ ሕግን የክስ መመስረቻ ጊዜ ጥያቄን ተቃውመው የተከራከሩ ሲሆን÷ በዚህም ምርመራ ተጠናቋል በተባለበት ደረጃ ላይ የተጠርጣሪ ተሳትፎ ተለይቶ አልቀረበም፣ ከኤምባሲና ከደህንነት ሰራተኞች ጋር በጥምረት የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት ነው ተብሎ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው አዲስ ፍሬ ነገር ነው፣ በዐቃቤ ሕግ ሰነድ ለማጣራት ተብሎ የቀረቡ ምክንያቶች ከመጀመሪያ ጀምሮ በፖሊስ ሲገለጹ የነበሩ ናቸው የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።

ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች ተጨማሪ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

ይህ የማይሆን ከሆነም ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ከተረከበበት ሕዳር 17 ጀምሮ ታሳቢ የተደረገ አጭር ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጥልን በሚል ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ትናንት ከሰዓት በኋላ በነበረው ቀጠሮ ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ የተረከበውን መዝገብ እና የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት ጊዜ እንደሚያስፈልገው መታመኑን በመጠቆም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ከተረከበበት ከሕዳር 17 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version