Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማይካድራ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ተፈጽሟል ተብሎ በተከሰሱት ላይ ምስክር ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በማይካድራ ከተማ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ተፈጽሟል ተብሎ በተከሰሱት ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

በነ ተክአ ባህታ የክስ መዝገብ የተካተቱ አጠቃላይ 202 ተከሳሾች መካከል 80 ያልተያዙ ሲሆን በአድራሻቸው አለመገኘታቸውን ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ፖሊስ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

ቀሪዎቹ ከ15ኛ እስከ 35ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እና 202ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱ ተከሳሾች መካከል መምህር ጃንቦ ብርሀነ፣ ገ/መድህን አብርሃ፣ ኪሮስ ሲሳይ፣ ሀፍቶ ካሳይ፣ ወ/ሮ አለምፀሀይ አሰፋን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ቀርበው እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በማይካድራ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ተፈጽሟል ተብሎ በቀረበው የወንጀል ክስ የካቲት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በነበረው ቀጠሮ ያልቀረቡ እነ አማኑኤል ኪሮስ ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ትዕዛዝ በመስጠት የቀረቡት የተከሳሾችን ግን በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተባቸውን ክስ ዝርዝርን በችሎት በንባብ አሰምቶ ነበር።

በክሱ እንደተመላከተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1ሀናለ 35:38 እና አንቀጽ 240/2 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ከ1ኛ እስከ 15ኛ ያሉ ተከሳሾች ከጥቅምት 14 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በነበሩ ቀናቶች በከተማዋ በተለያዩ ቀበሌና ቀጠናዎች በመደራጀት ገጀራ፣ መጥረቢያ፣ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅና በመታጠቅ እንዲሁም በመምራት፣ በማነሳሳትና በመደገፍ ጭምር ማንነትን መሰረት ያደረጉ የግድያ ወንጀሎች ተሳትፎ አድርገዋል የሚል ዝርዝር በአንደኛ ክስ ላይ ቀርቧል።

በ2ኛ ክስ ከ16ኛ እስከ 202ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን የሚመለከት ሲሆን በየደረጃው በራሳቸው ፍቃድ ተሳታፊ በመሆን ከ219 በላይ ዜጎችን በመታወቂያና በቤት በማንነት በመለየት በተለያዩ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ጥቃት በማድረስ ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ፣ አስከሬናቸውን በግሬደር ጭኖ በመውሰድና በጅምላ በመቅበር ተሳትፎ አላቸው በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ማስፈሩን ለችሎቱ በንባብ አሰምቶ ነበር።

በተጨማሪም በክስ ዝርዝሩ ላይ ከ217 በላይ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና በሌሎች በ10 ሴቶች ላይ ደግሞ ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆኑን እንዲሁም 17 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም የማድረግ የወንጀል ተግባር መፈጸሙን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ማስፈሩን በችሎቱ በንባብ ተሰምቷል።

አጠቃላይ ተከሳሾች በተሳትፎ ደረጃቸው የእያንዳንዳቸው ሚና ተጠቅሶ ተደራራቢ 44 ክስ ነበር በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው።

በወቅቱ 22 ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የዋስትና ጥያቄ በማቅረባቸው ዐቃቤ ሕግ የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና እንደማያሰጥ ገልጾ ክርክር ተደርጓል።

ችሎቱም በሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረው ቀጠሮ አንድ ተከሳሽ ከተከሰሰችበት የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ አንጻር የዋስትና መብት በማክበር ቀሪ 21 ተከሳሾች ግን የተከሰሱበት አንቀፅ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ከ7 እስከ 20 ዓመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ነው በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን አልተቀበለም።

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በዝርዝር በጽሁፍ አቅርበው ነበር።

በዚሁ በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 መሰረት በህገ-መንግስቱ ስር የተደነገጉ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች የማክበርና የማስከበር ሀላፊነትና ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ ህገ-መንግስቱንም ጭምር የመተርጎም ስልጣን የተሰጠውና በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 9/1 ድንጋጌ መሰረት ይህ ፍ/ቤት ይህን ጉዳይ የመመልከት ስልጣን የለውም የሚሉ የህገ-መንግስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ፍሬ ነገሮችን አካተው በዝርዝር የክስ መቃወሚያ አቅርበው ነበር።

በአጠቃላይ የቀረበው የወንጀል ክስ ከህገ-መንግስታዊ ጥሰቶች አንጻር ጉድለቱ እስካልታረመ ድረስ ክሱ በፍርድ ቤቱ መቀጠል የለበትም በማለት ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸው ጠይቀው ነበር።

በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩል ደግሞ የፍርድ ቤቱን ስልጣን በሚመለከት የፌደራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመመልከት ስልጣን እንዳለው ጠቅሶ አጠቃላይ ዝርዝር መልስ አቅርቦ ነበር።

የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ብለው የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸው ውድቅ እንዲደረግ በዐቃቤ ሕግ በኩል ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የህገ-መንግስት ትርጉም የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ለህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መልስ እንዲሰጥበት ከሌሎች መዝገቦች ጋር ልኮት ነበር።

የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ የክስ መቃወሚያዎች ተመርምረው የፍርድ ቤት ስልጣንን በሚመለከት በዚሁ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የመመልከት ስልጣን እንዳላቸው ተገልጾ የተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርገዋል።

ሌሎች የማስረጃ ፍሬ ነገር ጉዳዮችን በሚመለከት የቀረቡ የክስ መቃወሚያዎችን ግን በፍርድ ቤቱ በቀጣይ በማስረጃ የሚረጋገጡ ይሆናሉ ተብለው ውድቅ የተደረጉ ናቸው።

ቀደም ሲል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና ህገ-መንግስት ጉዳዮች ችሎት ተብሎ ይጠራ የነበረውና በአሁን ወቅት ስያሜው ተሻሽሎ 2ኛ የህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተብሎ ለተሰየመው ችሎት የተከሳሾችን የዕምነት ክህደት ቃል መዝግቧል።

በዚህም ተከሳሾቹ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግም የምስክሮች ቃል እንዲሰማለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ከጥር 1 እስከ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version