Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተቋማት ትኩረትና ቅንጅታዊ አሰራር ማነስ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ጫና እያሳደረ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቋማት ትኩረትና ቅንጅታዊ አሰራር ማነስ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ብሔራዊ የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ-ግብር አስተባባሪ ኮሚቴ የድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ የዝግጅት ትግበራ ፕሮጀክት ሥራን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ከድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ ጋር የሚጣጣም የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጂ ለመቅረጽ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ሃብት ካላቸው 20 ቀዳሚ ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው÷ ይህንን ሃብት ለመጠበቅ የበርካታ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ በተቋማት ዘንድ የሚስተዋለው የትኩረትና ተባብሮ የመስራት ውስንነት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።

የኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመንገድና መሰል መሰረተ ልማቶች የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱና ወደ ትግበራ ከመገባቱ አስቀድሞ ብዝሃ ሕይወት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ አጥንቶ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ የሚፈለገውን ውጤት አለማስመዝገቡን ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም ተቋማት የሚሰሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ከግምት ያስገቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ብዝሃ ሕይወትን ከመጠበቅ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ፣ የገበታ ለሸር፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተምሳሌትነት የሚነሱ ናቸው ብለዋል።

ተቋማትም ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ በጎ አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version