አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ሕዝብ የሰላም መፍትሄ የሚሻ በመሆኑ ፅንፈኞችን በማረም ሰላሙን ሊጠብቅ ይገባል ሲል የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
ቢሮው የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች አስመልክቶ መልዕክት አስተላፏል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንደህዝብ ከገባንበት አሁናዊ ፈተና በጋራ ለመውጣት ሰላም የወል ግባችን ሊሆን ይገባል!
መንግስት ከትናንት የተረከባቸው እና አሁናዊ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከአመራር ለውጥ ጀምሮ እስከ ውስጥ አሰራር ሪፎርም በማድረግ በጊዜ የለኝም ስሜት እየሰራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ሕዝብን ባልተገባ ፕሮፓጋንዳ በመናጥ የውስጥ ሰላሙን የሚያናጉ አካላት በተደጋጋሚ ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ የሰላም ጥሪ ቢደረግም አሁንም በክፉ ድርጊታቸው ቀጥለዋል።
እነዚህን የህዝብ ጥያቄዎች ሽፋን በማድረግና ችግሮቹን ለግል እና ለቡድን የፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ የሚያደርጉ አካላት የክልሉ ህዝብን ለማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት ከመዳረግ ዉጭ አንዳች ጠብ የሚል ለውጥ አያመጡም።
ይሄን ያልተገባ እንቅስቃሴ መግታትና ማረም የመንግስት የምንጊዜም ተቀዳሚ ስራ ነው።
ህዝባችን በተዛባ መረጃ ሰላሙን እንዳይጠብቅ ጦር የሚሰብኩ ነገር ግን የጦር ሜዳ የማይገኙ የሞት አዋጅ ነጋሪዎች ፣የህብረተሰብን የአንድነት ውል ለመናድ ሌት ከቀን የሚሰሩ፣ የደም ነጋዴዎችና የግጭት ጠማቂዎች ሰለባ ባለመሆን እንደህዝብ ሰላሙን መጠበቅ ይገባዋል።
በመሆኑም የአማራ ህዝብ መንግስታዊ ስርአትን አበክሮ የሚያውቅና የሰላም መፍትሄ የሚሻ ሕዝብ በመሆኑ ፅንፈኞችን በማረም ሰላሙን ሊጠብቅ ይገባል።
የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ