አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በየደረጃው የተጠናከረ የሕዝብ ንቅናቄ ፈጥሮ መሥራት እንደሚገባ ጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጀሉ አሳሰቡ።
“የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል” በሚል መሪ ሐሳብ 36ኛው የዓለም ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።
በተለይም በሽታው አምራቹን ኃይል የሚጎዳ በመሆኑ በክልሉ ቀጣይ ልማትና እድገት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በአከባበሩ ላይ የተገኙት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም በክልሉ የኤች አይ ቪ ቫይረስን የስርጭት መጠን ለመግታት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ተግተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቫይረሱ በደማቸው ለተገኘባቸው ወገኖች አስፈላጊውን የፀረ ኤች.አይ.ቪ ሕክምና አገልግሎትና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ጭምር አመራሩ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ቀኑን በክልሉ በልዩ ትኩረት ማክበር ያስፈለገውም በሽታውን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በይበልጥ ለማጠናከር በማሰብ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ታች ኮንግ ÷ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የበሽታው ስርጭት መጠን ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አኳያ ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት 3 ነጥብ 69 መሆኑንና ይህም ከሀገር አቀፍ የስርጭት መጠን 2 ነጥብ 82 መብለጡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚሰራው ሥራ በጤና ተቋማት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት እንዲሠሩ ጠይቀዋል።