አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና አጀንዳዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን በኮፕ 28 ጉባዔ አሳይታለች ሲሉ የኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ተወካይ ናሙኮ ኮቪች ገለጹ።
ናሙኮ ኮቪች ኢትዮጵያ በኮፕ28 ጉባዔ በራስ ዐቅም የዓየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያከናወነችውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አካፍላለች ብለዋል።
በዚህ ተሞክሮ ሀገሪቷ ችግሮችን የሚቋቋም ጠንካራ የተግባር ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደምትገኝ መመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የዘርፉን አጀንዳዎች በሙሉ ዐቅም ለመተግበር ተጨባጭ የለውጥ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኗንም ተረድቻለው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በአረንጓዴ ልማት ማዕቀፍ 50 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እያከናወነች ያለችው ተግባር በተሞክሮነት እንደሚወሰድ አውስተው÷ ይህም ሁለትዮሽ ጥቅም እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ከሚተከሉት ችግኞች ገሚሱ ለምግብነት የሚውል መሆኑን ገልጸው÷ የዓየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ጎን ለጎን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተግባራዊ እርምጃ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የተናገሩት፡፡
እንደ ሌማት ትሩፋት ያሉ መርሐ-ግብሮችም በዚህ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸውና ቀጣይነት ያለው የሥርዓተ-ምግብ ሽግግርን ለመከወን የተያዘውን ሀገር አቀፍ ውጥን ኢትዮጵያ በኮፕ 28 ጉባዔ ማሳየቷን ገልጸዋል፡፡
የዓየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

