Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሕዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ የአመራር ልቀት አካዳሚ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ።

ስልጠናው በተቋማዊ ሪፎርም፣ በሥነ ምግባርና በለውጥ አመራርነት እንዲሁም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለጣቢያችን የላከው መግለጫ ያመላክታል።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፥ የፖሊስን የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት ለሰው ሃብት፣ ለወንጀል መከላከልና ለምርመራ ሥራ የሚያግዙ ዘመናዊ ትጥቆችና ቴክኖሎጂዎች እየተሟሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻለው በፖሊስ ተቋም ውስጥ ጠንካራ አመራር በመፍጠር መሆኑን በማውሳትም፥ የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራርና አባላት ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ስልጠናው የተቋሙን ተልዕኮ መነሻ በማድረግ መካሄዱን ጠቅሰው፥ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና አባላት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

ሰልጣኞችም ከስልጠናው ያገኙትን የአመራርነት ጥበብ በመጠቀምና ማህበረሰቡን የፀጥታው ባለቤት እንዲሆን በማድረግና በቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባር ላይ በማተኮር ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ ተናግረዋል።

Exit mobile version