Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በቂ ትምህርት ወስዳለች – መሐመድ አብዱላኢ ሙሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ከተከናወነው ተግባር ጅቡቲ በቂ ትምህርት ወስዳበታለች ሲሉ የሃገሪቱ የአካባቢ ጥበቃና የዘላቂ ልማት ሚኒስትር መሐመድ አብዱላኢ ሙሳ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው ኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ያዘጋጀችውን አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ/ፓቪሊዮን የሃገራት መሪዎች፣የጉባኤው ተሳታፊዎች እየጎበኙት ነው።

ፓቪሊዮኑን የጎበኙት ሚኒስትር መሐመድ አብዱላኢ ሙሳ እንደገለጹት÷በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ኢትየጵያ ባለፉት አምስት አመታት በአረንጎዴ ልማት ያከናወነቻቸው ተግባራት ትልቅና የሚያስደንቁ ናቸው።

በቀጣይም ጅቡቲ በኢትዮጵያ የተከናወነውን የአረንጎዴ ልማት ተግባራዊ ለማድረግ በአገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር በኩል የተጠናከሩ ስራዎችን በትኩረት እንደምትሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በትራንስፖርትና በኤሌክትሪክ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃ ላይም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጎዴ ልማት ስራ ለጅቡቲ በርካታ ችግኞችን በመለገስ የአረንጎዴ አሻራ እንዲስፋፋ ያደረገችው አሰተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

Exit mobile version