አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች፣ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት መሆኑን ባንኩ አስታወቀ፡፡
ባንኩ ይህን አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ÷የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ በህዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም እትሙ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት ላይ ተነሥቶ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች፣ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል ብሏል፡፡
በመሆኑም ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዮን በተመለከተ የቀረበ ዕቅድ ካለመኖሩም ባሻገር እስከ አራት ሰዓት በፈጀው ውይይት ወቅት በብሔራዊ ባንክ የተነገረ ነገር እንደሌለ ህብረተሰቡ ተረድቶ ከዚህ ዐይነት አሳሳች መረጃ እንዲጠበቅ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የሪፖርተር ጋዜጣም በሚቀጥለው እትሙ ይህንኑ የሐሰት ዘገባ እንዲያርም እየጠየቀ በዚህ አሳሳች ዘገባና አሉባልታ ምክንያት በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ሰው ሠራሽ ጭማሪ ተቀባይነት እንደማይኖረውና ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡