Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዝኃነትን በእኩልነት በሚያስተናግድ መልኩ መቃኘት አለበት ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ብዝኃነትን በእኩልነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ቅኝትን መፍጠር እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ከነገ ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ ለአምስት ተከታታይ ቀናት “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።

አምስቱ ቀናትም÷ ሕዳር 25 የወንድማማችነት፣ ሕዳር 26 የብዝኀነት፣ ሕዳር 27 የአብሮነት፣ ሕዳር 28 የመደመር ቀን እንዲሁም ሕዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራሉ፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ የሕገመንግሥትና የፌደራሊዝም አስተምኅሮ ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ኢትዮጵያ የብዝኃነት ሀገር ብትሆንም ብዝኃነትን በእኩልነት የሚያስተናግድ ሥርዓት ሳይገነባ መዝለቁን አንስተዋል።

ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ምኅዳርም ብዝኃነትን የልዩነት መፍጠሪያ የማድረግ እንጂ ለሀገራዊ አንድነት ማጠናከሪያ እንዲሆን አላደረገም ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን በትክክል የሚገልፅና ወደፊት የሚያሻግር፣ ብዝኃነትን በእኩልነትና በፍትሐዊ ውክልና ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ ቅኝት መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘው የቆዩትን አብሮነት በማጽናት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያጎለብቱና በሕገ መንግሥቱና በኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓቱ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሥራት እነደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን እርስ በርስ መተዋወቂያ፣ የባህል መድመቂያ መድረክ ከመሆኑ ባለፈም፥ ለሀገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ አዳዲስ ዕይታዎች ላይ ውይይት በማድረግ መፍትሔ የሚቀርብበት ዐውድ እንዲሆን መሥራት ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version