Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራች ነው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ሆና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የገንዝብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ  ከዱባዩ የአየር ንብረት ጉባዔ ጎን ለጎን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ቀጣና ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት  በፋይናንስ ለመደግፍ እና ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስለመሆኑ ተመላክቷል፡

በተጨማሪም ውይይቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ቀጠናዊ ውህደትን ለማምጣት እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የቀጣናው መንግስታት የጋራ አቋም እንዲይዙ የሚያስችል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በመድረኩ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት የገንዝብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ሆና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ የጋራ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ÷ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የአረብ ልማት ማስተባበሪያ ቡድን(ቢኤዲኢኤ) የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ የኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካዮችን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሳተፋቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version