Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ታጣቂዎች መንግሥት የሰጠውን የሰላም ዕድል በመጠቀም ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሕግ ማስከበር የመጣውን ለውጥ ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተመላከተ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ ዋና አማካሪ ይርጋ ሲሳይ በክልሉ ስለመጣው ለውጥና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት የተጠናከረ እርምጃ አበረታች ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

ከክልል እስከ ወረዳ ያለውን የመንግሥትና የፀጥታ መዋቅሮች እንደገና በማደራጀትና በማጠናከር በተከናወነው ሥራ አሁን በአብዛኛው አካባቢዎች ሰላም መስፈኑንም አስረድተዋል።

በቀጣይም ከክልል እስከ ቀበሌ የፖሊስና የሚሊሻ ኃይል ቅንጅታዊ አሠራርን በማዳበር፣ በስልጠና በማጠናከር ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም በተሟላ ሁኔታ የማስከበር ሥራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ሕዝባዊ መድረክ በማካሄድ መግባባት ተፈጥሯ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኮቹም ሕዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ሕግ ይከበርልንና የተሟላ የመንግሥት አገልግሎት ልናገኝ ይገባል የሚሉ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ የመንግሥት ሠራተኛውን በማስተባበር የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በተቀናጀ መልኩ ርብርብ በማድረግ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

በሰላም ማስከበር የተገኘውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገረ የክልሉ ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊትና ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡

ታጣቂዎች የያዙትን የተሳሳተ መንገድ አዋጭ አለመሆኑን በመገንዘብ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰጠውን የሰላም ዕድል በመጠቀም ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀረበውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ሰላምና ልማትን ለማደናቀፍ በሚጥሩት ላይም የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ይርጋ አስታውቀዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version