Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ሕብረብሔራዊነትን ያጠናክራል- ረ/ኮሚሽነር  ደራርቱ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ሕዳር 26፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር አብሮነትንና ሕብረ ብሔራዊነትን ያጠናክራል ስትል የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር  ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ”ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እየተከበረ ነው።

በዛሬው ዕለትም በዓሉን አስመልክቶ ‘የብዝኃነት’ ቀን በሚል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ባህል፣ ማንነት፣ ወግ እና ትውፊት የሚያንጸባርቁ ትርዒቶችን አቅርበዋል።

በዚህ ወቅት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸችው÷ በዕለቱ የቀረቡት ባህላዊ ትርዒቶች ኢትዮጵያ የአስደናቂ ባሕል መገኛና የብዝሃነት ተምሳሌት መሆኗን ያሳያል።

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላቸውን፣ ማንነታቸውንና እሴታቸውን የሚሳዩበትና  ልምድ የሚጋሩበት መሆኑን የገለፀችው ደራርቱ፥ የአሁኑ ትውልድና የቀጣዩን ትውልድ አንድነትና ትስስር ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለውም ገልፃለች፡፡

ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ የሕብረብሔራዊነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶችን ማጎልበት እንደሚያስችል አመልክታለች።

የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህልን ይበልጥ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝባለች።

አንድነቷ የተጠበቀችና ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍም እያንዳንዱ ትውልድ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርባለች።

Exit mobile version