Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች በጠንካራ እሴት በመመራት በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ ጥሪ አቀረቡ።

“የሀገር ግንባታ መሰረታውያን” በሚል ርዕስ ለማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

አቶ ታዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዜጎች የጋራ ማንነትና ጥቅም ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች ሚና የጎላ ነው።

የብሔር፣ የእምነት፣ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃሳብ ማንነትን የያዘ ብዝሃነት ቢኖረንም በሀገር ግንባታና በጋራ እሴቶች ላይ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ አለብን ብለዋል።

በዚህም የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች ሀገራዊ ማንነትና ዘላቂ ጥቅምን አውቀው በትክክለኛ እሴት በመመራት በሀገር ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም ህዝቡን በማስተሳሰርና አንድነትን በማጠናከር ላይ መስራት አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፥ በዚህ ዙሪያ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች የጋራ አረዳድ ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቅን ልቦና በጎ ስራ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ስንሻው፥ ማህበራዊ ሚዲያን እንዴት ለሀገር ግንባታና ሰላምን ለማፅናት ማዋል እንችላለን በሚለው ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና የማህበረሰብ አንቂዎች በሃይማኖትና በማንነት ላይ ትኩረት በማድረግ አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚሸረሽሩ አጀንዳዎች ላይ ሲሰሩ እንደሚስተዋል ገልጸው፥ ይኸ ዓይነቱ አካሄድ ለሀገር ግንባታ አይጠቅምም ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version