Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የህዝቡ ትብብርና እገዛ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።

ለተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች “ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፣ በህብረት እንታገል” በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረው 20ኛው የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል እና የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ሙስና የህዝብ ብሎም የሀገር ጠላት በመሆኑ የጋራ ትግል ማድረግን ይጠይቃል።

በመሆኑም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የሙስና ወንጀልን መከላከል በተወሰነ አካል ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የህዝቡ እገዛና ጥረት ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል።

የህዝብን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በሙስና ወንጀል የተያዙ 146 ተከሳሾች በህግ ተጠያቂ ሆነው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አንስተው፤ በተጨማሪም በርካታ የመንግስትና የህዝብ ሃብቶች ከመዝባሪዎች ተመላሽ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

ሙስናን በመከላከል ሂደት በእስካሁኑ ሂደት ጥቆማና መረጃዎችን በመስጠት ህዝቡ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይ በተለይም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግልጽ አሰራር በመዘርጋት ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ሊከላከሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

Exit mobile version