Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ትውልዱ የሀገሩን እና የጥቁር ህዝቦችን ክብር ለማስቀጠል አፍሪካዊ ተቋማትን መደገፍ እንደሚገባው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሁኑ ትውልድ የሀገሩን እና የጥቁር ህዝቦችን ክብር ለማስቀጠል አፍሪካዊ ተቋማትን መደገፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት ዓለም አቀፉ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ፣ የቅርስ እና የትምህርት ማዕከል ዋና ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ መክፈቱን ሲያበስሩ ነው።

የዓለም የጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣ የቅርስና የትምህርት ማዕከል የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፣ ከፍተኛ የመንግስት እና የአፍሪካ ህብረት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የማዕከሉ መስራች አባላትና ሌሎች ተጋባዥ እግዶች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል።

በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ንግግር ያደረጉት አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለጹት፥ ማዕከሉ መቀመጫውን በኢትዮጵያ ማድረጉ የጥቁር ህዝቦችን ታሪክና አበርክቶ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ተጨባጭ ስራዎችን እውን ለማድረግ ያስችላል።

መጭውን ትውልድ በአፍሪካዊ እውቀት ለመቅረጽ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች በትምህርት እና ምርምር ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ማዕከሉ ዋና መቀመጫውን በኢትዮጵያ ማድረጉ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ቤት መሆኗን አዲስ አበባ ደግሞ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚያፀና መሆኑንም አመላክተዋል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች በበኩላቸው የማዕከሉ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ላበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ መቀመጫውን አዲስ አበባ ማድረጉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በፍሬህይወት ሰፊው

Exit mobile version