Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ግለሰብ በማስፈራራት ግማሽ ሚሊየን ብር ተቀብለዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 791 ነጥብ 78 ግራም ወርቅ ይዞ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብን በማስፈራራት ግማሽ ሚሊዮን ብር ተቀብለዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥቆማው እንደደረሰው እነዚህ ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ሲያከናውን ቆይቷል።

ተከሳሾቹ 1ኛ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ሹፌር የነበረው ም/ሳጅን ሞላ ተሾመ፣ 2ኛ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ኮንስታብል አይናዲስ አበበ፣ በግል ስራ የሚተዳደረው አበበ እንየው እና የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባል የነበረው መሐመድ ዘበን አሊ ናቸው።

በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ  በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

በዚህም የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ 1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባል ሆነው በመስራት ላይ እያሉ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆነውና በድለላ ስራ ከሚተዳደረው 3ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ሲሆን በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ስሙ ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በወርቅ አቅራቢነት ስራ ላይ የተሰማራውን የግል ተበዳይ መጠኑ 791 ነጥብ 78 ግራም ወርቅ ይዞ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተጠቁመን ነው የመጣነው ህገ ወጥ ወርቅ ይዘሀል በማለትና 2ኛ ተከሳሽ መታወቂያ በማሳየት ወደ መገናኛ አካባቢ መውሰዳቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ የፌዴራል ፖሊስ መኪና እያሽከረከረ 4ኛ ተከሳሽ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ፣ ሽጉጥና መገናኛ ሬዲዮ በመያዝ ሁሉም ተከሳሾች በጋራ በመሆን የግል ተበዳዩን ይዘውት የፖሊስ መኪና ላይ በመጫን ወደ መገናኛ አካባቢ በመውሰድ ግለሰቡ የያዘው ወርቅ ሕገ ወጥ ነው በማለት ወርቁን እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው በክሱ ተገልጿል።

በዚህ ጊዜ የግል ተበዳይ ፍቃድ እንዳለውና ወርቁም ህጋዊ እንደሆነ ሲገልፅ 1ኛና 4ኛ ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት ሊያስቀጣህ ይችላል ወንጀል ነው በማለት በማስፈራራት የግል ተበዳዩ 2 ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

የግል ተበዳይም 500 ሺህ ብር ልስጣችሁ ባለበት ጊዜ ተከሳሾች በሞባይል ባንኪንግ አስተላልፍልን በማለት እንዲተላለፍላቸው ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህ ጊዜም የግል ተበዳዩ ለሚያውቀው ለሌላ አንድ ግለሰብ ስልክ በመደወል 300 ሺህ ብር 1ኛ ተከሳሽ በስሙ በከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ እንዲተላለፍ ማድረጉ በክሱ ተገልጿል።

1ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከዚህ ከተላለፈለት ገንዘብ ላይ 120 ሺህ ብር እና 25 ሺህ ብር ለ4ኛ ተከሳሽ ያስተላለፈለት መሆኑ በክስ ዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል።

እንዲሁም ቀሪውን 200 ሺህ ብር ደግሞ የግል ተበዳዩ ለሌላ ጓደኛው ወደ ሆነው ግለሰብ ስልክ በመደወል 200 ሺህ ብር 3ኛ ተከሳሽ በስሙ በከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር እንዲተላለፍ በማድረግ ባጠቃላይ 500 ሺህ ብር ተከሳሾች ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመገልገል ከግል ተበዳይ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ተከሳሾቹም ከጠበቃ ጋር ተማክረው ለመቅረብ ለፊታችን ሰኞ ታሕሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version