አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ ተባባሪ አካላት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቀቀ፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ በነበረው ስልጠና በክልሉ ከሚገኙ 12 ዞኖች የተውጣጡ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
ከስልጠናው በተጨማሪ ሰልጣኝ ተባባሪ አካላቱ በተሳታፊዎች ልየታ ሂደትና አተገባበር ላይ በግብዓትነት የሚወሰዱ አስተያየቶችን ለኮሚሽኑ አባላት አቅርበው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
በስልጠናው ተባባሪ አካላቱ ባደረጓቸው የቡድን ውይይቶችም የክልሉን ዓውድ መሰረት በማድረግ ከየማህበረሰብ ክፍሉ ተሳታፊዎችን ስለሚለዩባቸው መንገዶች ምክክር አድርገዋል፡፡
በቀጣይም ተባባሪ አካላቱ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመሄድ በኮሚሽኑ ከተለዩት የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎችን በመለየት ረገድ ሂደቱ ተዓማኒ እንዲሆን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡