አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ከኮፕ28 ጉባኤ ጎን ለጎን በዘላቂ የኃይል ተደራሽነት ዓለም አቀፍ ጥምረት ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተገለጸ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ የኢፌዴሪ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና በሞሮኮ ኢነርጂ ሽግግር እና ዘላቂ ልማት ሚኒስትር ለይላ ብናሊ እንዲሁም በሞሮኮ የዘላቂ ኃይል ኤጀንሲ ታሪክ ሃማኔ ተፈርሟል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ዘላቂ የኃይል ተደራሽነት ጥምረት ለመፍጠር፣ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ እና ጠንካራ ትብብርን ለመመስረት ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው የሞሮኮ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ለደቡብ-ደቡብ ትብብር በተለይም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የአየር ንብረት ለውጥን እና የዘላቂ ልማት ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅና ለመስጠት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ሰነዱ ሁሉን ያካተተ እና ለሁሉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ክፍት እንዲሆን እንደሚደነግግ የሞሮኮ ኢነርጂ ሽግግር እና ዘላቂ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ዘላቂ የኃይል ተደራሽነት ጥምረቱ ራሱን የቻለ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ያለው እና የእውቀትና የልምድ ልውውጥ እና በዘላቂ ሃይል መስክ የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ሁሉም ወገኖች ተስማምተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለዘላቂ ኢነርጂ ተደራሽነት ጥምረት የእውቀት፣ የልምድ ልውውጥ እና የክህሎት ሽግግር ስራዎችን የሚደግፍ የስልጠና ማዕከል በማቋቋም ቋሚ ዋና መስሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ እንዲሆን መደረጉም በሥምምነቱ ተካቷል።
ቋሚ ዋና መሥሪያ ቤቱን በሞሮኮ ያደረገው የዘላቂ ኢነርጂ ተደራሽነት ጥምረት ሴክሬታሪያት የተቋሙን በጀት የሠራተኞች ምደባ፣ የጽሕፈት ቤቱ አደረጃጀትና አሠራር፣ የተልዕኮዎቹን አፈጻጸም ጨምሮ የበጀት አፈፃፀም ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!