Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል – የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ሌሎች ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐ-ግብር ዓመታዊ የልማት ጉባዔውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ÷ የኢንዱስትሪ ልማት የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና በሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት ሪፎርም አጀንዳ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መጠሰቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህን ተከትሎም የዘርፉን ውጤታማነት የሚያጠናክሩ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም የዘርፉን እድገት የሚያሳልጡ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ተደርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጥቅሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ለዘርፉ ልማት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ቻሩ ቢስት በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማስፋት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የገቢ ምርቶችን በመተካት በአጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ትልቅ ዐቅም እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርሐ-ግብርም ዘርፉን ለማጠናከር የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

Exit mobile version