Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ዓየር ኃይል የተመሰረተበት 88ኛ ዓመት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ዓየር ኃይል የተመሰረተበት 88ኛ ዓመት እየተከበረ ነው፡፡

የምሥረታ ዓመቱ እየተከበረ የሚገኘው ‘በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ ዓየር ኃይል’ በሚል መሪ ሐሳብ ነው፡፡

ከምሥረታ በዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና መገናኛ ብዙኃን ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የዓየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የጉብኝቱን ዓላማ በተመለከተ ባደረጉት ንግግር÷ ዓየር ኃይል በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እና በውጊያ መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ የሚመጥን መሆኑን ለማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዓየር ኃይል የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ማስገንዘብ የጉብኝቱ ዓላማ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡

ዓየር ኃይል በርካታ የጀግንነት ተግባራትን ሲፈፅም መምጣቱን አስታውሰው÷ ዛሬም በተቋሙ ሪፎርም መሰረት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማለፍ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሱን ለማዘመን ብሎም አስተማማኝ ዓየር ኃይል ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የዓየር ኃይል የበረራ ክልል፣ አዲስ የተገነባው ስታዲየም፣ የመዝናኛ ክበብ እና የሰው አልባ አውሮፕላን ተጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይም የጦር ጀት አውሮፕላን፣ ዙ 23 የጦር አውሮፕላን፣ ሄሊኮፕተር እና አንቶኖቭ አውሮፕላን ለጎብኚዎቹ የዓየር ላይ ትርዒት አሳይተዋል፡፡

የዓየር ላይ ትርዒቱም ጥቁር አንበሳ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል መባሉን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version