አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ፎረም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ፎረሙ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ በኢንዱስትሪው ባሉ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመሩ በማድረግ የመጓተት ችግርን ለመፍታት በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ ታይቷል፡፡
ከዚህ ባለፈ ለፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት የሆነውን የባለሙያዎች ዓቅም ውስንነትን ለመሙላት ስልጠናዎች ተሰጥተዋል ብለዋል።
በዚህም ከ20 ሺህ በላይ ፈፃሚዎችን ማሰልጠን እንደተቻለ ጠቅሰው÷ ከ400 በላይ ባለሙያዎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ዓለም ዓቀፍ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናትናኤል ጌታሁን (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ ፎረሙ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የንግድ ትስስር፣ የልምድ ልውውጥ፣ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም ቀጣይ ዕድሎች ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮንስትራክሽን ባለስልጣንና የክልሉ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ማህበር ያዘጋጁት ፎረሙ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር መስፍን ነገዎ እና የኦሮሚያ ክልል ኮንስትራክሽን ዘርፍ አማካሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመራኦል ከድር