Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ የኢንቨስትመንት ተመራጭነትን ለማስቀጠል ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል አሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢውን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮችና ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄዱ ነው።

የሰላም የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ሕዝቡንም የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በአካባቢው አልፎ አልፎ የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባም ነው  አቶ አረጋ ያስገነዘቡት፡፡

በደብረ ብርሃንና አካባቢዋ የተጀመሩና ገና ለማስጀመር በዕቅድ ላይ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ያለምንም መስተጓጎል እንዲቀጥሉ ሕዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ለሰላሙ ጠንክሮ እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡

በመንግሥትና ሕዝብ የጋራ ጥረት በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ከተቻለ የከተማዋን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት አጠናክሮ ማስቀጠል የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነውም ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብእሸት በበኩላቸው÷ ከተማዋ በኮማንድ ፖስት እንድትመራ ከተደረገ ወዲህ የጸጥታ ሁኔታው በእጅጉ ተሻሽሏል ብለዋል።

በተገኘው ሰላምም በባለሃብቶች ለቀረቡ 80 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የምልመላ፣ የመረጣና ፈቃድ የመስጠት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

መስፈርቱን ላሟሉ 36 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መሬት ተሰጥቷ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በአበበ የሸዋልዑል

Exit mobile version