Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻችንን እንወጣለን – የሐይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ከደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሐይማኖት አባቶችም÷ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁና ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ወጣቱን በመምከር ሰላም እንዲወርድ በእምነት ተቋማት ጭምር እናስተምራለን፤ ወላጅም ልጁና ቤተሰቡን በመምከርና አጥፊውን በማረም ለሰላም መስፈን ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሰላም የሚያደርገው ጥረት እንዳስደሰታቸውና ይህንም እንደሚደግፉ ጠቁመው÷ በአንጻሩ ግጭት ለሚፈጥሩና ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩትን እንደሚቃወሙ አስገንዝበዋል፡፡

የመንግሥት የሰላም ጥሪ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አሳውቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው÷ በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር በሰላም ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛና ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

አውቀውም ሆነ ተሳስተው ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎችን በመምከርና በመገሰጽ የሐይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሕግ የማስከበር ተግባር በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ የተሳሳቱትን መክሮ ወደ ሰላም ማምጣትና ልማትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አሳሙኤል ሞላልኝ÷ የጥፋትን መንገድ የተከተሉ ግለሰቦችን አባቶች መክረውና ገስጸው እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚረጋገጠው በመንግሥት ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የተሳሳቱ ወጣቶችን ከሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር መክረን ወደ መደበኛው የዕለት ተዕለት ሥራቸው እንዲመለሱ እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version