Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቀጣዮች 10 ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ቅዝቃዜው ሊያይል እንደሚችል ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 10 ቀናት በአንዳንድ የሰሜን፣ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምሥራቅ፣ የመካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖረው ተመላከተ፡፡

እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በአሥሩ ቀናት ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የዓየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ ዓየር በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ቀጣይነት እንደሚኖረው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የዓየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን÷ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይም በሰሜን፣ በምሥራቅና በደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁሟል፡፡

ለዝናብ መፈጠር ምቹ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ የተሻለ ጥንካሬ ሲኖራቸው÷ በዚሁ መሠረት በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብና ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ የዝናብ ገጽታ እንደሚኖራቸውም ነው የተመላከተው፡፡

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በተለይም በምዕራብ እና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ የጉጂና የቦረና ዞኖች፤ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ ከሶማሌ ክልል የዳዋ፣ የሊበንና የአፍዴር ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሲኖራቸው፤ በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በተጨማሪም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች፤ የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ጎንደር እና የሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ የሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፣ የምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ኢሉአባቦር፣ አርሲ፣ የመካከለኛው፣ የምሥራቅ እና የደቡብ ትግራይ ዞኖች እንዲሁም ከአፋር ክልል ዞን 2 እና 4 ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ባሉት ቀናትም በጥቂት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚስተዋል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

Exit mobile version