አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች በአውራጅ እና ጫኝ ስራ በአዲስ መልክ ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑን የከተማ አስተዳዳሩ ሰላምና ጸጥታ አስተዳዳር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ሚዴክሳ ከበደ እንደገለጹት÷ በእቃ አውራጅና ጫኝ ዘርፉ ሕግና ደንብ ከወጣ በኋላ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ቀንሰዋል፡፡
ሕጉ ከመውጣቱ በፊት በዘርፉ የሚታዩ አለመግባባቶች ለአካባቢው ሰላም ማጣት ዋነኛ ምክንያት እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በአዲሱ ሕግና ደንብ ላይ የሁለቱ አካላት መብት እና ግዴታ በግልጽ በመስፈሩ አልፎ አልፎ በነበረው ልማድ ሲሰሩ በነበሩ አካላት ላይ በሕግ እስከ መጠየቅ መደረሱንም ተናግረዋል።
እስካሁን ከ300 በላይ ማህበራት እና ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች በሁሉም ክፍለ ከተማ ወጣቶች በአውራጅና ጫኝ ስራ ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑን አቶ ሚዴክሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
የተደራጁ ወጣቶች ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ስለመሆኑ ጠቅሰው፥ በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ እና የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ አኳያም ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም ክፍለ ከተማ ያሉ ማህበራት እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ወቅቱን ያገናዘበ ክፍያ ለሚሰሩት ሥራ ሒሳብ እንዲከፍሉም በመመሪያው መሰረት ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል።
በሲሳይ ጌትነት