አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ለዛሬ ብቻ ደስታቸውን የሚፈልጉ፣ ለነገ የማያስቡ እና ለነገ ይሆናል የማይሉ ሰዎች ችግሩ ይዞባቸው የሚመጣው ተጽዕኖ ይኖራል፡፡
የሥነ ልቦና ባለሙያው ካሌብ ታምራት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ለዛሬ ብቻ የማሰብ ሥነ-ልቦናን አስመልክተው ቆይታ አድርገዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአንዳንድ ወጣቶች ላይ የራስን ብቻ ፍላጎት ማሟላት፣ ዛሬን ተደስቶ ማለፍ ብቻን በማሰብ እና ነገ ለራሱ ይጨነቅ የሚሉ መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የዛሬን በመተው ለነገ ብቻ በማሰብ ራሳቸውን የሚጎዱ እንዳሉም ነው የሥነልቦና ባለሙያው የሚናገሩት፡፡
ሆኖም ግን ሁለቱም ልክ እንዳልሆኑም ነው የሚገልጹት፡፡
በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ለዛሬ ብቻ ደስታቸውን የሚፈልጉ፣ ለነገ የማያስቡ እና ለነገ ይሆናል የማይሉ ሰዎች ችግሩ ይዞባቸው የሚመጣው ተጽዕኖ ብዙ እንደሆኑም ነው የገለጹት፡፡
አንድ ግለሰብ ማህበረሰቡ ላይ የሚወስዳቸው አመለካከቶች እንደሚኖሩት የሚገልጹት ባለሙያው፥ ግለሰቡ አመለካከቱን ከራሱ ህይወት አንጻር የተረጎመበት መንገድ ለእርሱ አስፈላጊ እንደሆነም ያስረዳሉ።
በዚህም ግለሰቡ ወይ እራስ ወዳድ እንዲሆን አልያም ዛሬን ሣይኖር ለነገ ብቻ እንዲጨነቅ በማድረግ ሊቀርጸው እንደሚችል አልያም ደግሞ ዛሬን በመኖር ለነገ በማሰብ የህይወት መንገዱን ማስተካከል እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
ስለነገ ካላሰቡ ባልታሰበው ኑሮ ነገን ይኖራሉ ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ካሌብ ታምራት፥ የሚፈጠረው እያንዳንዱ እክልም ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
ከግለሰብ በተጨማሪም ቤተሰብ፣ ማህበራሰብ አልፎም ሀገር በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ውስጥ ይገባሉ ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም እራሱ ግለሰቡ የሚፈልገውን ነገር ራሱን በማዳመጥ፣ በማወቅ፣ መመርመርና መረዳት አለበትም ነው ያሉት፡፡
በዚህም ለነገ ህይወት በመጨነቅ ሣይሆን በማስተዋል ነገሮችን በመመርመር እቅዶችን በማውጣት ዛሬን ብቻ ሣይሆን ለነገም ሥንቅ ማኖር እንደሚቻልም ተናግረዋል የሥነ-ልቦና ባለሙያው፡፡
ዛሬን እየኖሩ ነገን እያሰቡ የተሻለ ነገር መስራት እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ።