Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ2016 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ÷ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሀገር ደረጃ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ከተጀመሩ 5 ዓመታት መቆጠሩን ያወሱት ሃላፊው÷ ለአብነትም የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጠቅሰዋል፡፡

በክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኙ ልምዶችን ከመቀመር ጎን ለጎን የወጣቶች ስብዕና ማዕከላት ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ፕሮግራሞችን ቀርጾ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ጠቁመው÷ ወጣቶችን ለመገንባት የሚያግዙ ተቋማትን ማጠናከር ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አርሻሎ አርካሌ በበኩላቸው÷ የክልሉ ወጣቶች ለሚያነሷቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለዩ 12 ዘርፎች ልዩ ልዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ማብራራታቸውን የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version