Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ሀገር ዜጎች በመስጠት ወንጀል የተጠረጠሩ 60 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ሀገር ዜጎች በመስጠትና ሠነድ አልባ ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 60 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ክሱን የመሰረተው የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ በአንድ ተከሳሽ ላይ ብቻ 1 ሺህ 169 ገጽ ሠነዶችን ኮፒ ለፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር በኩል አቅርቧል።

ተጠርጣሪዎቹ ከደላላና እና ከተለያዩ ሀገራት ዜጎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር÷ ከሕግ ውጪ ጉቦ እየተቀበሉ ለውጭ ዜጎች በመስጠት፣ ከሕግ አሠራር ውጪ ቪዛ በመስጠት፣ ሠነድ አልባ ዜጎችኝ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣትና በማስገባት፣ አልሸባብን ጨምሮ ለሽብር ቡድን አባላት ፓስፖርት እንዲወስዱ በማድረግ፣ ሕጋዊ ተመዝጋቢዎችን ማጉላላት የሚሉ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው ምርመራ ሲካሄድባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

በዚሁ መሠረት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጉዳይ የቀድሞው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገምበታ እና የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት የውጭ ዜጎች ቁጥጥርና ቆንፅላ ጉዳዮች ቀድሞው ምክትል ዳይሬክተር ጂላሎ በድሩን ጨምሮ በሌሎችም ተጠርጣሪዎች ላይ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ዳይሬክቶሬት ዘርፍ ምርመራ ሲከናወንባቸው ቆይቷል፡፡

ምርመራው መጠናቀቁን ተከትሎም÷ በተለያየ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቦች ተካተው በነበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ባቀረበው የ 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ መሰረት ዛሬ አጠቃላይ 15 የሙስና ወንጀል ክስ ተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ መስርቷል።

ክሱ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች መካከልም ከ 30 በላይ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ፍርድ ቤቱ ማስረጃ ተመሳክሮ አለመጠናቀቁን ጠቅሶ በቀጣይ ተጠናቀው የሚደርሱ ክሱ ዝርዝሮችን ለመጠባበቅ ለፊታችን ሰኞ ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version