Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዩኔስኮ-ሁዋዌ  ፕሮጀክት ለትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ መሳሪዎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩኔስኮ-ሁዋዌ ፕሮጀክት ለትምህርት ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ÷ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እና ሁዋዌ የዲጂታል ትምህርትን ለማገዝ ያሳዩትን ቁርጠኝነት እና የትምህርት ሚኒስቴርን ዲጂታል አካታች ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይ በመደገፋቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የአይሲቲ መሳሪያዎቹ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ግብአቶችን እንዲፈትሹ፣ እውቀታቸውን ከመማሪያ መጽሀፍት በላይ እንዲያዳብሩ እና ከዓለም አቀፋዊ መረጃዎች እና ተሞክሮዎች ጋር እንዲገናኙ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የዩኔስኮ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኔስኮ  ከሁዋዌ ቴክኖሎጂ እና ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ  እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የአይሲቲ ቁሳቁሶቹ ቀደም ብለው በተለዩ እና በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ ተናግረዋል፡፡

ቁሳቁሶቹ የራሳቸው ሙሉ መለዋወጫዎች ያላቸው 480 ታብሌቶች፣ 48 አክሰስ ፖይንት እና 24 ስማርት ቦርዶች  ሲሆኑ 300 ሺህ ዶላር እንደወጣባቸውም አስረድተዋል፡፡

የዩኔስኮ ሁዋዌ ፕሮጀክት በፈረንጆቹ 2022 የተመሰረተ ሲሆን ከተለያዩ ሀገራት ትምህርት ሚኒስትሮች ጋር በመተባባር በኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ እና ጋና እየተተገበረ እንደሚገኝ ከትምህርት ሚኒስቴር ያኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version