Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ሲሆን÷ በጉባዔው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

የቀረበውን የውሣኔ ሀሳብ መነሻ በማድረግ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።

ለቀረበው ጥያቄና አስተያየት በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 1310/2016 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

“የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ” የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በሀገር ሉዓላዊነትና በዜጎች ደህንነት ላይ ስጋት የሚፈጥሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ለመቆጣጠርና ገደብ ለመጣል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡

በተያያዘም በኢትዮጵያ መንግስት እና በሊባኖስ መንግስት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመው ስምምነት ረቂቅ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 1311/2016 ሆኖ በሁለት ተቃውሞ በሁለት ድምፀ- ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መንግሥት መካከል የተደረገውን በሁለትዮሽ ወታደራዊ ቴክኒካዊ ትብብር ወቅት የተገኙ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች እና ንብረቶች የጋራ ጥበቃ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1313/2016 ሆኖ በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እና በፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ በንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መነሻ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄና አስተያየት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1312/2016 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

Exit mobile version