አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ስብዕናችንን የቀረጸ፣ የሀገር ፍቅር ስሜት ያወረሰንና ለሀገር እንድንኖር መሠረት የሆነን ተቋም ነው ሲሉ የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ተናገሩ።
የአቪዬሽን ትምህርታቸውን በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት የተከታተሉት የአየር ኃይል ጡረተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ያሬድ ሽፈራው÷ በ1977 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን እንደተቀላቀሉ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ ወደ ግንባር በመሰለፍ በሲስተም ኦፕሬሽንና ሌሎች ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
በበረራ ቴክኒሺያንና ሌሎች ሙያዎች ለረጅም አመታት ሀገራቸውን ያገለገሉት ሌላው የማኅበሩ አባል ማስተር ቴክኒሺያን ዮሐንስ አሰኒ÷ በተቋሙ ስብዕናቸውን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋዕኦ እንደነበረው ተናግረዋል።
በጡረታ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ባለሙያዎች የሥርዓት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ተቋሙን እንዲለቁ ቢደረጉም ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጥሪ ተደርጎላቸው ተቋሙን ዳግም አደራጅተው ድል እንዲመጣ ካደረጉ ባለሙያዎች መካከል ናቸው።
የአየር ኃይሉ ከምስረታው ጀምሮ በዘመናዊ አሠራር እንደተገነባ ገልጸው÷ ተቋሙ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በማስጠበቅና እግረኛውን በማገዝ የጦር ሠራዊቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ተናግረዋል።
የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሀገር ያገለገሉ፣ በሀገር ፍቅር የነደዱ፣ ግዳጃቸውን በብቃትና በጀግንነት የተወጡ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደሆኑ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ዘንድ እንደ ብርቅ የሚታይና የሀገር ኩራት የሆነ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬም ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን እየታጠቀ የቀጠለ እንደሆነ አንስተዋል።
የወቅቱ አየር ኃይል የቀድሞ ሠራዊት አባላትን እንደ ቤታቸው ቆጥረው እንዲንቀሳቀሱና እንዲያገለግሉ በማድረጉ ተቋሙ እንደ ባለውለታ እንደሚቆጥሩት ገልጸው÷ማኅበራቸው ከተቋሙ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።