Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል እየተፈጠሩ ያሉ የህዝብ ግንኙነት መድረኮች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው – ብ/ጄ ዘውዱ ሰጥአርጌ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ከኀብረተሰቡ ጋር እየተፈጠሩ ያሉ የህዝብ ግንኙነት መድረኮች መልካም ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ደሴ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ገለጹ።

ኮማንድ ፖስቱ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ በብርጋዲየር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ የተመራ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ኮማንድ ፖስቱ በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ የመሳሪያ አዘዋዋሪዎችን በማጥፋትና የማህበረሰቡን ሰላም በአጭር ጊዜ በመመለስ ረገድ ያደረገው ርብርብ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ይህም ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር የተደረገ ክትትል ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።

የፀጥታ መዋቅሩን በፍጥነት በማደራጀትና ወደ መደበኛ ስራው በመመለስ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የሚደርሱ የግዳጅ ጫናዎችን በመቀነስ ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ብርጋዲየር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ተናግረዋል።

በዚህም የአካባቢውን ወጣቶች በማደራጀት ሰላማቸውን እንዲያስጠብቁ መደረጉን ገልጸዋል።

ህዝቡ ሰላሙን ለማጽናት የሚረዱ አደረጃጀቶች ውስጥ በመግባት አካባቢውን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ተነግሯል።

በመድረኩ የኀብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴን ለማሻሻል እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ የህግ ማስከበር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version